Government Statement
ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ09/09/05ውብ አዲስ አበባን የመፍጠር ራዕያችንን ምቹ የመኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎች ለማስተላለፍ እቅዳችን በተጠናከረ ሁኔታ በተግበር እናረጋግጣለን
መዲናችን አዲስ አበባ ለዘመናት ተከማችተውባት በኖሩ ዘርፈ ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አማካኝነት እድገቷ ተገቶ ቆይቷል፡፡ የአፍሪካና የአለም አቀፍ ተቋማት መገኛ የሆነችው ከተማችንን የተጋረጡባትን የእድገት ማነቆዎች በመበጣጠስ በልማት ጎዳና ላይ መገስገስ ጀምራለች በህዝቦች ተጋድሎ ዲሞክራሲያዊና ሕገ መንግስታዊ ስርአቷን ያፀናቸው ሀገራችን ከዳር እስከ ዳር ያቀጣጠለችው የልማት ችቦ ከተማችንንም ማሞቅ እና ማድመቅ ከጀመረ እነሆ ጥቂት አመታት መቆጠር ጀምረዋል፡፡ በተለይም ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ ከተማችን አዲስ አበባ በሁሉም የልማት ዘርፎች የጀመረቻቸው ስር ነቀል ለውጦች ውጤት ማስመዝገብ ይዘዋል፡፡ መዲናችንን ውብ፣ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ አስተዳደሩ በያዘው ትግል ያረጁና የተጎሳቆሉ የከተማዋን ስፍራዎች በአዲስ ለመለወጥ ተስፋ ሰጪ እምርታዎች ማስተዋል ተችሏል፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ ከሀገራችን ከተሞች በተሻለ ደረጃ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስባት ከተማ መሆንዋ ይታወቃል፡፡ የዚህ ካፒታል መሰረቱም የመዲናችን ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በከተማችን ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻልና ይህንንም ፍትሐዊነት በህዝቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ስለሆነም የከተማችን ነዋሪ ዋንኛ ጥያቄ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት መንግስት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የከተማችን ነዋሪዎችን የዘመናት የመኖሪያ ቤት እጦት ጥያቄን ለመፍታት አስተዳደሩ ባደረገው ያላሰለሰ ትግል ባለፉት ጥቂት አመታት ብቻ ከ1ዐዐ ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፡፡ በዚህም ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን የመጠለያ ጥያቄ መፍታት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከ95 ሺ በላይ ቤቶች በግንባታ ላይ ያሉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ያልተላለፉ ከ89 ሺህ በላይ ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎችም ከ24 ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ዘርፍ አስተዳደሩ እስከ አሁን ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ያደረገ ሲሆን የመረሃ ግብሩ የጎንዮች አላማ በሆነው የስራ ዕድል ፈጠራ ከ148 ሺ በላይ ለሚደርሱ ወገኖች በተለያየ ደረጃ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ አስተዳደሩ በከተማችን ለዘመናት የተከማቸውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በ1996 በጀመረው የተቀናጀ የመኖሪያ ቤት ግንባታ በርካታ የመዲናችን ነዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከከተማዋ እድገትና ልማት ጋር በተያያዘ የሚነሳው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ አስተዳደሩ ሌሎች የተሻሉ አማራጮችን በመቅረፅ የሕብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ይበልጥ እንዲንቀሳቀስ አድርጓታል፡፡ በመሆኑም ቀደም ተብሎ ከተጀመረው 2ዐ/8ዐ የተቀናጀ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ጎን ለጎን ድሃ ተኮር የሆኑ የ1ዐ/9ዐ ቤቶችና ለመካከለኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን የሚያቅፉ የ4ዐ/6ዐ እና የሕብረት ስራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማህበራትን ያካተቱ የመኖሪያ ቤት መርሃ ግብሮችን በመቅረፅ በቅርቡ የከተማችንን ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ የምዝገባ ስራውን በአዲስ መልክ ለማካሔድ ዝግጅት መጀመሩ ይታወቃል፡፡ አስተዳደሩ በእነዚህ የመኖሪያ ቤት ልማት ኘሮግራሞች ነዋሪው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እድል ያመቻቸ ሲሆን ዜጎች ተገቢና ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች በማድረግ የሀገራችንን እድገት ለማፋጠን እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የከተማችን ነዋሪዎችን በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች በዋናነት የገቢ አቅማቸውን በማሳደግ እና ከገቢያቸው በመቆጠብ የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የቤት ችግሮቻቸውን መፍታት የመርሃ ግብሩ ሌላኛው አላማ ነው፡፡ አስተዳደሩ ቀደም ብሎ የከተማዋን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ባደረገው እንቅስቃሴ በ1997 ዓ/ም 453 ሺህ የሚሆኑ አመልካቾችን በመመዝገብ ከ1ዐዐ ሺህ ያላነሱት የመኖሪያ ቤት በመገንባት ማከፋፈሉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ምዝገባ ከተካሔደ በኋላ በሚፈጠሩ ተፈጥሮአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች አማካኝነት ቀሪዎቹ ተመዝጋቢዎች ያሉበትን ሁኔታ በዳግም ምዝገባ ማጥራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም በወቅቱ የተመዘገቡ እና የመኖሪያ ቤት እድሉ ያልደረሳቸው ዜጎች በነባር አመልካቾች ምድብ ለ2ዐ/8ዐ የመኖሪያ ቤት መርሃ ግብር ዳግም የሚመዘገቡበት ስርአት ተዘርግቷል፡፡ ሌሎች አዲስ ተመዝጋቢዎች አስተዳደሩ ካዘጋጃቸው አራት አማራጮች ማለትም የ1ዐ/9ዐ ዝቅተኛ የወር ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የ2ዐ/8ዐ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች፣ የ4ዐ/6ዐ መካከለኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች እና በህብረት ስራ ማህበራት የመኖሪያ ቤቶችን መገንባት በሚሉ ምድቦች ውስጥ አቅምንና ፍላጎትን በማመዛዘን በአንዱ ላይ ብቻ በመመዝገብ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡ አስተዳደሩ የነዋሪውን ችግር ለመፍታት በዘረጋቸው የመኖሪያ ቤት ግንባታ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ላለፈው አንድ አመት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ዝግጅት ምዝገባው የሚመራበትን መመሪያ ከማውጣት ጀምሮ ምዝገባው የሚካሔድበትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መቅረፅ ችሏል፡፡ በመሆኑም የምዝገባውን ስርአት አስመልክቶ በከተማዋ ሁሉም ወረዳዎች ለሚገኙ አራት ሺህ ለሚሆኑ ኃላፊዎች፣ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከ15ዐዐ በላይ ዳታ ኢንኮደሮች በኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች ማዘጋጀት ተችሏል፡፡ በዚህም ምዝገባውን በከተማዋ ሁሉም ወረዳዎች ወጥነት ባለው መንገድ ማካሔድ የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መዘርጋት ተችሏል፡፡ ለዚህም ስራ አስተዳደሩ ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሕብረተሰቡን መረጃ በአስተማማኝ እና በተቀላጠፈ መልክ ማደራጀት የሚያስችል ስርአት አዋቅሯል፡፡ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት አስተዳደሩ እያካሔድ ባለው በዚህ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ የከተማችን ነዋሪ የተለመደ ድጋፉን በማበርከት ለመርሃ ግብሩ ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም በቀጣዩ ሰኔ 3 ቀን 2ዐዐ5 ዓ/ም በይፋ ምዝገባው በሁሉም የከተማችን ወረዳዎች የሚጀመረውን የ1ዐ/9ዐ እና የ2ዐ/8ዐ የነባር እና አዲስ የመኖሪያ ቤት አመልካቾች ምዝገባ ከመካሔዱ በፊት ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ምዝገባውን በሰከነ እና በተረጋጋ ሁኔታ ማካሔድ ይኖርበታል፡፡ ነዋሪዎች ለምዝገባው የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በአግባቡ በመረዳት ቀደም ካለው አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ማለትም የነዋሪነት ማረጋገጫ የመታወቂያ ወረቀት፣ የቁጠባ ማረጋገጫ የባንክ ደብተር እንዲሁም የትዳር ሁኔታዎችን የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን በማጠናከር ምዝገባው የተቀላጠፈና የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምዝገባዎቹ በቅደም ተከተል የሚካሔዱ ሲሆኑ ከሰኔ 3 እስከ 2ዐ የሚካሔደው የ1ዐ/9ዐ እና የ2ዐ/8ዐ መርሃ ግብር ምዝገባ መጠናቀቅ በኋላ በቀጣይ የሐምሌ ወር አጋማሽ የመኖሪያ ቤት ማህበራት ምዝገባ ይካሄዳል፡፡በመቀጠልም በቀጣዩ የነሐሴ ወር የ4ዐ/6ዐ የመኖሪያ ቤት መርሃ ግብር ምዝገባ እንደሚካሔድ ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ዜጎች አስቀድመው አቅማቸውን በመፈተሽ ከመርሃ ግብሩ በአንዱ ላይ ብቻ እንዲመዘገቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ከፊደራል መንግሥት ጋር በመተባበር በታላቁ መሪ የተቀየሰውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በመኖሪያ ቤት ግንባታ ዘርፍ የያዘውን 17ዐ ሺህ ቤቶች በእቅዱ ዘመን ገንብቶ በማጠናቀቅ ከ85ዐሺ በላይ ለዜጎች ለማከፋፈል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ መላው የከተማችን ነዋሪም የመዲናችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ አሰተዳደሩ ከያዛቸው የልማት ስራዎች ጋር የተለመደ ትግሉን በማቀናጀት አዲስ አበባችን ለዘመናት የተከማቹባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከስሩ በመናድ መዲናችንን ውብ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ የማድረግ ጥረታችንን በጋራ አጠናክረን እንድንቀጥል አስተዳደሩ በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
|
||
|
































