Joomla TemplatesBest Web HostingBest Joomla Hosting

ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ 19/04/2005

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ

ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ                                                                                   

 

የሃገርና የህዝብ አገልጋይነት እንዲጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

 

በአንድ ሃገር የመልካም አስተዳደር በአስተማማኝ መስፈን በሃገሪቱ ያለውን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ በመንግስት አካላትም ሆነ በዜጎች ያለአግባብ የመጠቀምና መጥቀም አስተሳሰብና ድርጊትን በብቃት ለመከላከልና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡

 

ከዚህም አልፎ በዝቅተኛ ደረጃ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ተሰሚነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ሲሆን የመንግስት አካላትም ትክክለኛና ለውጤታማነት የሚያበቃ ውሳኔ ለመስጠት ያስችላቸዋል፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማክበርና ለማስከበርም ወሳኙ ጉዳይ መልካም አስተዳደርና መርሆቹን በብቃት መፈጸም ነው፡፡

 

መልካም አስተዳደር በየትኛውም ሁኔታ ተጠያቂነት፣ ግልጽነትና ለህዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ የመስጠትን፣ ህዝብን በሁሉም ሃገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች የማሳተፍን፣ የህግ የበላይነትንና ሌሎች መሰረታዊ መመዘኛዎችን የማሟላት ጉዳይ ነው፡፡

 

የመንግስት አካላትና ተቋማት በህዝብ የተሰጣቸውን ዴሞክራሲያዊ ስልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ የሚፈፅሙበት ካልፈፅሙ ግን የሚጠየቁበት አሰራር መሆኑም ግልጽ ነው፡፡

 

ከዚህም ጐን ለጐን በልማትና ኢኮኖሚው መስክ ውጤታማ ለመሆን መልካም አስተዳደርን ማስፈን የግድ ይላል፡፡ የልማት ሥራዎች በህዝብ ጥያቄና ተሳትፎ የሚሰሩ መሆን ይገባቸዋል፡፡ የሥራዎቹ አፈፃፀም ከእቅድ አንስቶ ህዝቡን ማሳተፍ፣ በውጤታማነቱም ሆነ በችግሮቹ ዙሪያ መግባባትና ለመፍትሄዎቹ በጋራ መስራትን ይጠይቃል፡፡

 

 

ህዝብን የማያሳትፍ፣ ለህዝብ ምላሽ የማይሰጥ የትኛውም የልማት እቅድ ውጤቱ ያማረ ሊሆን አይችልም፡፡ በአንፃሩ የህዝብ እምቅ አቅም በመጠቀም የሚከናወን ልማት ከመነሻው ጀምሮ የህዝብ ድጋፍ ያለው በመሆኑና የህዝብ ክትትልና ድጋፍ ስለማይለየው በውጤቱ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ህዝብና ሁሉም የሚረካበት ይሆናል፡፡

 

በከተማችን አዲስ አበባ ከሚሰሩ የልማት ሥራዎች ጐን ለጐን የህዝብን ጥያቄ እና ፍላጐት እንዲሁም ድጋፍ በመጠየቅ ሕዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ተሳታፊ ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

 

መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይ መርሁን የመከተል ብቻ ሳይሆን የመተግበርም በመሆኑ በሁሉም ደረጃ ያሉት የአስተዳደሩ አካላት የሚተገብሩትና እርስ በርስና ከህዝብ ጋር የሚጠያየቁበት እንዲሆን በየአመቱ በዋና እቅድነት በመያዝ እየተሰራ ሲሆን አፈፃፀሙም በየጊዘው እየተገመገመና ማስተካከያዎች እየተደረጉ ይገኛል፡፡

 

በዚህ ሂደት በተለያዩ ዘርፎችና የመዋቅር ደረጃዎች የከተማዋን ልማትና እድገት መፋጠን በብቃት የሚያግዙ፣ የህዝቡን ጥያቄና ፍላጐት ማርካት ያስቻሉና በማርካት ላይ የሚገኙ፣ ለከተማዋ አለም አቀፍና ሃገራዊ ገፅታ ከፍተኛ ድርሻ በማበርከት ላይ የሚገኙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

 

በተቃራኒው እነዚህን ገፅታዎችና ሚናዎች የሚያኮስሱ ሁኔታዎች መፈጠራቸውም አልቀረም፡፡ ለዚህም ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተያዘው 2ዐዐ5 በጀት አመት የነበሩ ችግሮች በከተማው አመራሮች ተገምግመው ማስተካከያ እንዲደረግባቸው መግባባት ተደርሷል፡፡ በተለይም በዋና ዋና ችግሮችና አፋጣኝ ምላሽ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችና በመካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅድ በመከፋፈል ችግሮቹን በመፍታት ሁሉም የአስተዳደሩ አካላት፣ ሠራተኞችና አመራሮች ተልእኳቸውን ወስደዋል፡፡

 

በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግሮቹ እንዲፈቱ የሰጠውን አመራርና ቁርጠኝነት በድጋሚ እያረጋገጠ የከተማችን ነዋሪዎችና በየዘርፉ ተገልጋዮች አሁንም የሚያጋጥሙትን ችግሮች በግልፅነትና በኔነት ስሜት እንዲያሳውቁ ያስገነዝባል፡፡

 ይህን የአፋጣኝ ጊዜና የረጅምና መካከለኛ ጊዜ እቅድ በብቃት ለማስፈፀምና የምንፈልገውን መልካም አስተዳደር በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስፈን እንዲቻልም በሁሉም ደረጃና በየዘርፉ ግንዛቤ የመፍጠርና እርስ በርስ ተቀናጅቶ እንዲሰራ የማድረግ ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡

 

በተለይም ሁሉም በየሙያውና ኃላፊነቱ ይህን ተገባር ለማስፈፀም እንዲችል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከእነዚህ አካላት መካከል የአስተዳደሩ የኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ድርሻም የላቀ በመሆኑ ይህን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡

 

በአጠቃላይ መልካም አስተዳደርን ማስፈፀም የመንግሥትና የመንግስት አካላትን ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠየቅ ቢሆንም ያለ ህዝብ ተሳትፎ ግን ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡ ጉዳዮ የሁሉንም ዜጐች የሃገርና የህዝብ አገልጋይነት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም አካላት በተለይም የከተማችን ነዋሪዎች፣ ባለሃብቶች፣ሠራተኞችና አመራሮች፣ የኮሙኒኬሽንና መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ በየሥራ ዘርፋቸው በጋራ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና እርስ በርስም ያሉ ችግሮችን በመደጋገፍና በመጠያየቅ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ልማትና መልካም አስተዳደር ለማረጋገጥ ከሚያደርገው ጥረት ጐን እንዲሰለፉ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

 

                                               የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

 

 
English (United Kingdom)
Addis looks like
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa
 • Addis Ababa