Government Statement
መስከረም 26 ቀን 2005 ዓ/ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ
ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
የተጀመረውን ልማት ለማፋጠን የሠላምና የዴሞክራሲ አማራጮችን በሚገባ ለመጠቀም እንረባረብ፡፡
ሃገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ለመሆኑ በእያንዳንዱ ዜጋ ኑሮ መሻሻል ከሚታየው ለውጥና በልማት መስክ እየተካሄደ ባለው ፈጣን ለውጥ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚህም አልፎ የአለማችን የኢኮኖሚ ተቋማትና ሃገራትም ይህን ለውጥና እድገት እየመሰከሩ ይገኛሉ፡፡
ይህ እድገትና ለውጥ ሊመዘገብ የቻለው ባለፉት ስርዓቶች የነበረው በዜጐች ላይ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታና ሌሎች ልዩነቶች ምክንያት ሲደረግ የነበረው ተፅእኖ አብቅቶ ሁሉም ዜጐች በልዩነቶቻቻው ተከብረውና እኩልነታቸው ተረጋግጦ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመራት በመቻላቸው ነው፡፡
ይህ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሁሉም ዜጐች በየራሳቸው ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ፣ ባህል፣ እምነት፣ ቋንቋቸውንና ሌሎችም መልካም ግለሰባዊ፣ ማህበረሰባዊና ሃገራዊ እምነትና ልማዶቻቸውን በነፃነት እንዲያራምዱ እድል የሰጠ በመሆኑ ነው፡፡
ከዚህም አልፎ በግል ወይም በአካባቢያቸው ሳይወሰኑ ስለሃገር እድገት፣ ልማትና አንድነት፣፣ ሠላምና በርካታ በጐ ተግባራት በእኔነት ስሜት የሚያስቡበትና በተግባርም የሚያረጋግጡበት እድል ሠፍቷል፡፡ ይህም በልዩነት አንድነት የከበረች ሃገር ለመመስረት ትልቅ እድል ሆኗል፡፡
አሁን ሁሉም የሃገራችን ዜጐች፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ይህን ስርዓት መፈታተን ማንነታቸውን እንደመፈታተን የሚቆጥሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የዚህ ስርዓት መቀልበስ የእያንዳንዱ ዜጋ ህልውና፣ የሃገር ህልውና፣ልማትና ሠላም የመቀልበስ ያህል ከባድ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እናም በየትኛውም ምክንያት ቢሆን ይህን ስርዓት ለመፈታተን የሚደረግን ጥረት መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሃገራችን ዜጐች በንቃት የሚጠብቁትና የሚከላከሉት ጉዳይ ነው፡፡
የሃገራችን ህዝብ ለእምነት ያለውን ቀናኢነት መጠቀሚያ ለማድረግ በመሞከር በአለማችን ስጋት የሆነውን የሃይማኖት አክራሪነትና የሽብር ተግባር ወደ ሃገራችን ለማምጣት የሚሹ ሃይሎችም ይህ ሙከራቸው እንደማይሳካላቸው ሊያውቁትና በሠላም አማራጭ የሚሹትን ጥያቄ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙንም ሆነ
የሌላውን እምነት ተከታይ በተለያዩ ጉዳዮች ማወናበድ፣ የሃይማኖቱን ጥያቄ ሳይሆን ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ በሃይማኖቱ ስም ማራመድ ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡
በመሆኑም በሃይማኖቱ ስርዓት የሃይማኖት ጉዳይ እንዲፈታ የተሰጠውን እድል መጠቀም ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረገውን የሽብር ሙከራና ተግባር ለማክሸፍ ግን በተለይም በከተማችን አዲስ አበባ ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ የሌሎች ሃይኖማት ተከታዮች በሠላም እምነታቸውን እንዲያራመዱ፣ በህገ-መንግስቱ የተቀመጠውን ከለላና ጥበቃ የማድረግ ተግባር እንደሚቀጥልበት፣ አለፍ ሲልም በህገወጥ ተግባር የተሰማሩትን ለህግ እንደሚያቀርብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስገንዘብ ይወዳል፡፡
አስተዳደሩ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሚያደርገው ማንኛውም ተግባርም በፀረ-ሰላም ሃይሎች እንደሚባለው ከህገ መንግስቱ የሚቃረን ሳይሆን ህገ-መንግስቱን የሚያከብርና የሚያስከብር መሆኑን ሁሉም አካላት ሊያውቁት ይገባል፡፡
በህገ-መንግስታችን አንቀጽ 27 የህዝብን ደህንነት፣ ሠላም፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የሞራል ሁኔታ፣ የዜጐችን መሰረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶች ለማረጋገጥ ሃይማኖትና እምነትን የመግለፅ መብት ሊገደብ እንደሚችል በግልፅ ሰፍሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት መንግስት እያደረገ ያለውም ይህን የህዝብና የሃገር ደህንነትና ሠላም የማስጠበቅ እንጅ እንደሚባለውና የሙስሊሙን ህብረተሰብ ለማወናበድ እንደሚጠቀሙበት መንግስት ጣልቃ እየገባ አይደለም፡፡
ህዝበ ሙስሊሙም ይህን ጉዳይ በሚገባ መረዳትና በቀቢፀ ተስፋ በመሙላት ያገኘውን ሠላምና ልማት ለማደናቀፍ የሚደረገውን ህገወጥ ተግባር ሊከላከል፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በተግባሩ እንዳይሳተፍ አስተዳደሩ ማሳሰብ ይወዳል፡፡ ከዚህ ይልቅም በሃይማኖቱ ሥርዓት መሰረት ችግሮቹን እንዲፈታና ህገ-መንግስታዊ መብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም ይጠይቃል፡፡
በነገው እለት እሁድ መስከረም 27 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. የሚካሄደው የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ምርጫም የሃይማኖቱ ተከታዮች እምነታቸውን በነፃነት በአግባቡ ለማራመድ የሚያስችላቸውን መሪ ለመምረጥ የሚያስችላቸው፣ የሃይማኖቱ ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት የሚካሄድ ምርጫ በመሆኑ በህገመንግስቱ የተረጋገጠውን የሃይማኖቶች እኩልነትና የእምነት ነፃነት መብት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
የምርጫው በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መከናወን ለአማኙ ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ለሃገር የዴሞክራሲ፣ የሠላምና የልማት መንገድም ታላቅ ብርሃን የሚፈነጥቅ በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉንም አማኞችና የከተማችንን ነዋሪዎች ቀናኢ ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
የሠላምና የዴሞክራሲ አማራጭ እንዲሁም የሃገራችንን ህገመንግስን ማክበርና ማስከበር የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ሁሉም ዜጋም ሆነ ሁሉም አካል የየራሱን ፍላጐት በግልም ሆነ በጋራ ማራመድና ማሟላት የሚያስችለው ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላም በኩል ለሃገር ተቆርቆሪ የሆነ ዜጋ ሃገር መልማት፣ የዜግነት ፍላጐት መሟላት የሚችለው በሠላማዊ አማራጭ ሲጠቀም ብቻ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል፡፡
በከተማችን የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችም በነገው እለት የሚካሄደውን የሃይማኖታቸውን መሪዎች የመምረጥ ተግባር በሠላማዊና ዴሞከራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡና እምነታቸውን በአግባቡ ለማራመድ የሚያስችላቸውን መሪ እንዲመርጡ፣ የከተማችን ነዋሪዎች፣የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮችና ሁሉም አካላትም ምርጫውን በሠላማዊ መንገድ ለማስፈፀምና የከተማችንን ልማት ለማፋጠን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እንዲሰሩ አስተዳደሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
































